ሦስተኛው የሸሪዓ ምንጭ፣ አመክንዮኣዊ የሕግ ምርምር (ኢጅቲሓድ)፡- ምንነቱና መገለጫዎቹ

Main Article Content

Alyu Abate

Abstract

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ከመጽደቁ በፊት ሲሰራባቸው የነበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ፍ/ቤቶች፣ በፌዴራል እና የክልል ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች እውቅና ሊሰጣቸውና ሊደራጁ እንደሚገባ የኢፌዲሪ ሕግ መንግሥት አንቀጽ 78(5) በሚያስገድደው መሠረት፣ ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ በሃገሪቱ ሲሰራባቸው የነበሩ የሸሪዓ ፍ/ቤቶች፣ በፌዴራል እና በክልል ደረጃ የአቋም ማጠናከሪያ አዋጆች ወጥተው፣ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ጠቅላይ ፍ/ቤት ድረስ እንደገና ተደራጅተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ፍ/ቤቶቹ በባለጉዳዮች ፈቃድ ላይ የተመሠረተ የዳኝነት ሥልጣን ያላቸው ሲሆን፣ የሚቀርቡላቸውን የግልና የቤተሰብ ግጭቶችን የሸሪዓ ሕግን ተፈጻሚ በማድረግ እልባት ይሰጣሉ፡፡ የሸሪዓ ሕግ ምንጮች በጥቅሉ ሦስት ናቸው፤ እነሱም ቁርአን፣ ሱናሕ እና ኢጅቲሓድ (አመክንዮኣዊ ምርምር) ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት የሸሪዓ ቀዳሚ ምንጮች በመለኮታዊ ራዕይ (ወህይ) የተገለጹ ሲሆን፣ በግልና በቤተሰብ ግንኙነቶች ላይ ቁጥራቸው ጥቂት የሚባሉ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ያካተቱ ሲሆን፣ አብዛህኞቹ የቁርአንና የሱናሕ ሕጎች የጥቅልነት ባህሪ ያላቸው እና በልዩ ልዩ የሕግ ዘርፎች ላይ አጠቃላይ እና ንዑስ የሸሪዓ ዓላማዎችን የሚቀይሱ ናቸው፡፡ ይህ ገጽታቸው፣ ዝርዝር የሸሪዓ ሕግ ማዕቀፍ (ፊቅሕ) እንደ ወቅቱ እና ማህበረሰቡ ተጨባጭ እውነታ፣ በሕግ ምርምር (ኢጅቲሓድ) አማካይነት እንዲዳብር መሠረት ጥሏል፡፡ በመሆኑም፣ ኢጅቲሓድ፣ በየትኛውም የሕግ መስክ ላይ የሸሪዓ ዝርዝር ሕግጋት ለመቅረጽ ዋነኛ ምንጭ በመሆን ሰፊውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ስለዚህ፣ ኢጅቲሓድ ዋነኛ የሸሪዓ ሕግ ምንጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምንነቱን እና መሠረታዊ መገለጫዎቹን በተመለከተ በመስኩ ምሁራን የሚነሱ ፍሬ-ሐሳቦች እና ጭብጦች በዚህ ጽሁፍ ተዳሰዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ሸሪዓ ፍ/ቤቶች የሕግ አተረጓጎም ጋር በተያየዘ፣ የሃገሪቱን ሙስሊም ማህበረሰብ ነባራዊ ሐቆች እና አካባቢያዊ እውነታዎች ያገናዘበ ትክክለኛና ተገቢ የሆነ የሸሪዓ ሕግ አተረጓጎምና አፈጻጸም እውን ለማድረግ፣ እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ በኢጅቲሓድ አማካይነት ማሻሻያዎችንና አዲስ የሸሪዓ ብይኖችን ለማስተዋዋቅ ይቻል ዘንድ፣ በኢጅቲሓድ እና በመርሆዎቹ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ መጨበጥ ያስፈልጋል፡፡ ሸሪዓን በትክክል ለመረዳት፣ ገዢነቱ በጊዜ እና በሕብረተስብ እውነታዎች ሳይገደብ፣ ተለማጭነቱን ማረጋገጥና የፍትሕ ዓላማዎቹን ማሳካት የሚቻለው በኢጅቲሓድ አማካይነት በመሆኑ፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት አግባብነት ያላቸውን የሸሪዓ የግልና የቤተሰብ ሕጎችን፣ እንዲሁም የኢስላም የፋይናንስና የባንክ ድንጋጌዎችና አሰራሮችን ከሃገሪቱ ተጨባጭ ጋር እንዲጣጣሙ በማድረግ ረገድ ወደፊት ለሚደረገው የሕግ አወጣጥ፣ ዳኝነትና ግጭት አፈታት እነዲሁም ጥናትና ምርምር ምንጭ እና መሪ በመሆን የሚያገለግለው ኢጅቲሓድ በመሆኑ፣ ይህ ጽኁፍ በዚህ ወሳኝ የሸሪዓ ሕግ ምንጭ ዙሪያ መሠረታዊ ግንዛቤ የሚያስጨብጭ ማብራሪያ ያቀርባል፡፡

Article Details

How to Cite
Abate, A. (2022). ሦስተኛው የሸሪዓ ምንጭ፣ አመክንዮኣዊ የሕግ ምርምር (ኢጅቲሓድ)፡- ምንነቱና መገለጫዎቹ. Jimma University Journal of Law, 11. https://doi.org/10.46404/jlaw.v11i0.3818
Section
Articles